ኢትዮጵያ 18 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር አዲስ የውጭ እርዳታና ብድር አግኝታለች
አዲስ አበባ, የካቲት 2 ቀን 2002 (አዲስ አበባ) -

ኢትዮጵያ በተያዘው ግማሽ የበጀት ዓመት 18 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር አዲስ የውጭ እርዳታና ብድር ማግኘቷን የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ሀገሪቱ የነደፈችው ምቹና አስተማማኝ ፖሊሲ ለውጭ ሃብት ፍሰቱ መጨመር ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑንም ሚኒስቴሩ ገልጿል፡፡

በሚኒስቴሩ የሕዝብ ግንኙነትና ኢንፎርሜሽን የሥራ ሂደት ሃላፊ አቶ ሃጂ ኢብሳ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት እርዳታና ብድሩ የተገኘው ከመልቲላተራልና ከመንግስታት የገንዘብ ምንጮች ነው፡፡

ከተገኘው ገንዘብ ውስጥ 11 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብሩ በእርዳታ ሲሆን 7 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብሩ ደግሞ ብድር መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ163 በመቶ ብልጫ ማሳየቱን ጠቁመዋል፡፡

እርዳታና ብድር የሰጡት የመልቲላተራል ተቋማትም ዓለም አቀፍ የልማት ማህበር፣ የነዳጅ ላኪ አገሮች ዓለምአቀፍ ልማት ፈንድ፣ ዓለም አቀፍ የግብርና ልማት ፈንድ፣ የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም፣ የተባበሩት መንግስታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት፣ ግሎባል ፈንድ እና ግሎባል ኢንቫይሮመንታል ፈንድ ናቸው ብለዋል፡፡

እንዲሁም ከተባባሪ መንግስታት ደግሞ ኔዘርላንድስ፣ ጣሊያን፣ ኖርዌይ፣ ፊንላንድ፣ ጃፓን፣ ቻይና፣ አየርላንድ፣ አሜሪካ እና እንግሊዝ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

ባለፈው ግማሽ በጀት ዓመት ለፕሮጀክቶችና ፕሮግራሞች ማስፈፀሚያ ከመልቲላተራልና ባይላተራል ምንጮች 13 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር የእርዳታና የብድር ፍሰት መገኘቱን ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ውስጥም 8 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብሩ በእርዳታ ሲሆን ቀሪው በብድር መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ይህም ባለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ተገኝቶ ከነበረው አጠቃላይ የውጭ ሃብት ፍሰት ጋር ሲነፃፀር የ35 በመቶ ብልጫ እንዳለው አመልክተዋል፡፡

ፈሰሱን ያደረጉት ዓለም አቀፍ ተቋማትም ዓለም አቀፍ የልማት ማህበር፣ የአፍሪካ ልማት ባንክ፣ የነዳጅ ላኪ አገሮች አለም አቀፍ ልማት ፈንድ፣ የአረብ ባንክ ለአፍሪካ የኢኮኖሚ ልማት ፈንድ፣ የኖርዲክ የልማት ፈንድ፣ ዓለም አቀፍ የግብርና ልማት ፈንድ፣ የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክና የአውሮፓ ሕብረት ናቸው ብለዋል፡፡

እንዲሁም የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም፣ የተባበሩት መንግስታት የሥነ-ሕዝብ ጉዳይ፣ የተባበሩት መንግስታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት፣ የዓለም ምግብ ፕሮግራም፣ ዓለም አቀፍ የምግብና የእርሻ ፕሮግራም፣ የተባበሩት መንግስታት ጥምር ፕሮግራም እና ግሎባል ፈንድም እንደሚገኙበት ገልጸዋል፡፡

አቶ ሃጂ እንዳሉት ከመንግስታት ምንጮች ከ3 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ የውጭ ሃብት ፍሰት የተመዘገበ ሲሆን ፈሰሱን ያደረጉት መንግስታትም አሜሪካ፣ ስዊድን፣ ጣሊያን፣ እንግሊዝ፣ ኦስትሪያ፣ ስፔን፣ አየርላንድ፣ ፈረንሳይ፣ ጃፓን፣ ሳዑዲአረቢያ፣ ኩዌት፣ ሕንድ፣ ፊንላንድ እና ቻይና ናቸው፡፡

ኢትዮጵያ ከፍተኛ የእዳ ጫና ያለባቸው ድሃ ሃገሮች የእዳ ማቃለያ ፕሮግራም ተጠቃሚ መሆኗን ጠቁመው በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራትም ከ70 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር በላይ የእድ ቅነሳ ተጠቃሚ መሆኗን አመልክተዋል፡፡

የእዳ ቅነሳውን ያደረጉትም የአፍሪካ ልማት ባንክ፣ የዓለም አቀፍ የግብርና ልማት ፈንድ እና የኖርዲክ ልማት ፈንድ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ሃላፊው እንዳሉት የተገኘው ገንዘብም ለግብርና፣ ለትምህርት፣ ለመንገድ ግንባታ፣ ለውሃ፣ ለጤና፣ ለኢንዱስትሪና ለሌሎች የድህነት ቅነሳ ፕሮግራሞች ይውላል፡፡

ከውጭ እየተገኘ ያለው እርዳታና ብድር እየጨመረ እንዲመጣ ሃገሪቱ የቀረፀቻቸው ምቹ ፖሊሲዎች ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡

ስ፡3፡40፣መ፡5፡00፣ያ፡45 ኤ6፡45

---END---

Headlines
ኢትዮጵያ 18 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር አዲስ የውጭ እርዳታና ብድር አግኝታለች
የአፍሪካ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴሮችና የኤች አይ ቪ ኮሚሽኖች በስነተዋልዶ ጤናና መብቶች ላይ ትኩረት ሰጥተው መስራት ይገባቸዋል፡-ፕሬዝዳንት ግርማ
(c) The Ethiopian News Agency