መለስተኛ ችሮችን በማጋነን ኢትዮጵያ እያስመዘገበች ያለውን ፈጣን እድገት ማጣጣል እንደማይቻል የማስታወቂያ ሚኒስቴር አስታወቀ
አዲስአበባ, ግንቦት 30 ቀን 2000 (አዲስ አበባ) - በአገራችን አንዳንድ ኪስ አካባቢዎች ተከስቶ ተገቢ ክትትል እየተደረገበት ያለውን የምግብ እህል እጥረት ሁኔታ ተጠቅመው አንዳንድ ለጋሽ ድርጅቶችና የመገናኛ ብዙሃን እያቀረቡ ያለው ሪፖርት ከእውነት የራቀ መሆኑን የማስታወቂያ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ኢትዮጵያ እያስመዘገበች ያለው ፈጣን እድገት በእንዲህ ዓይነት ፈጠራ አከል የተጋነነ ሪፖርት የሚጣጣል አለመሆኑንም ገልጿል፡፡

ሚኒስቴሩ " የአገራችንን ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ልማት መለስተኛ ችግሮችን በማጋነን ማጣጣል አይቻልም " በሚል ርእስ ዛሬ እንዳስታወቀው ከበልግ ዝናብ ጋር ተያይዞ ዘንድሮ በአንዳንድ የአገሪቱ ኪስ አከባቢዎች የተፈጠረውን የምግብ እጥረት አስመልክቶ አንድንድ ለጋሽ ድርጅቶችና ተቋማት እርዳታ ለማሰባሰብ የሚያቀርቡት ሪፖርት የተጋነነ እንዲሁም የአንዳንድ መገናኛ ብዙሃን ዘገባ ከእውነት የራቀና ግነት የተሞላበት ነው፡፡

ከድህነት ለመውጣት በሚደረገው የተጠናከረ ጥረት ባለፉት አምስት ዓመታት ባለሁለት አሃዝ የኢኮኖሚ እድገት መገኘቱን ያመለከተው ሚኒስቴሩ ይህንን ዕድገት አጠናክሮ ለመቀጠል መንግሥትና ህብረተሰቡ በቁርጠኝነት በመንቀሳቀስ ላይ መሆናቸውን ገልጿል፡፡

ምንም እንኳን ዘንድሮ የበልግ ዝናብ መስተጓጎሉ ተጽእኖ የፈጠረ ቢሆንም ይህን ተከትሎ በዘንድሮ የምርት ዘመን ጥሩ ውጤት ለማግኘት መንግስትና መላው አርሶ አደር ከፍተኛ ርብርብ እያደረጉ መሆናቸውንም አመልክቷል፡፡

ከበልግ ዝናብ መስተጓጎል ጋር ተያይዞ በተወሰኑ ኪስ አካባቢዎች የምግብ እህል እጥረት ቢከሠትም መንግሥት አስፈላጊውን ክትትልና ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ከቁጥጥር ውጭ ሊሆን እንደማይችል ማስታወቂያ ሚኒስቴር አብራርቷል፡፡

እንደሚታወቀው ከዝናብ መስተጓጉል ጋር ተያይዞ 14 ሚሊዮን ያህል ህዝብ ለምግብ እህል እጥረት በተጋለጠበት በ1994 እና 1995 ዓ.ም እንኳን መንግስትና ህብረተሰቡ ተባብረው ችግሩ የከፋ አደጋ ሳያስከትል በቁጥጥር ስር እንዲውል አድርገዋል ።

ይኸው ውጤት የኢትዮጵያ መንግስትና ሕዝብ ኃላፊነት ከሚሰማቸው ለጋሽ መንግስታትና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በመሆን ያስመዘገቡት እንደመሆኑ ሁሉም ወገኖች ሊመሰገኑበት የሚገባ እንደነበር አመልክቷል፡፡

የያኔው ልምድ የአሁኑን ዓይነት መለስተኛ ችግር በቀላሉ ለማለፍ የሚያስችል መሆኑ እየታወቀ አንዳንድ ድርጅቶች ለማጋነን የሞከሩበት ሁኔታ ተገቢ አለመሆኑን ሚኒስቴሩ ገልጿል፡፡

በተለይም በዓለምአቀፍ ደረጃ የነዳጅ ዋጋ መናርና ፈጣን እድገት ያስመዘገቡ አገሮች የፈጠሩት ከፍተኛ የምግብ ፍላጎት የምግብ ዋጋ ንረት እንዲከሠት ማድረጉ እየታወቀ በኢትዮጵያ የተለየ ሁኔታ እንደተፈጠረ አስመስለው አንዳንድ የመገናኛ ብዙሃን የሚያቀርቡት ዘገባም ሚዛናዊነት የጎደለው መሆኑን አስታውቋል፡፡

የመገናኛ ብዙሃኑ ያልተፈጠረ ሁኔታን በመጨመርና መለስተኛ ችግሮችን በማጋነን ማቅረባቸው የአገሪቱን ትትክለኛ ገፅታ እንደማያመለክትና የተዛባ እንደሆነ ገልጿል፡፡

መንግስትና ሕዝብ ፈጣንና ቀጣይነት ያለው ልማት በማረጋገጥ አገሪቱን ለመለወጥ የጀመሩትን ርብርበ አጠናክረው በመቀጠል በአዲሱ ሚሌኒየም የመጀመሪያዎቹ አስርት ዓመታት መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ ለመሰለፍ የጀመሩትን ጥረት አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ማረጋገጡ ነው ሲል ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡

ሪ 12፡45ያ1፡11

---END---

Headlines
መለስተኛ ችሮችን በማጋነን ኢትዮጵያ እያስመዘገበች ያለውን ፈጣን እድገት ማጣጣል እንደማይቻል የማስታወቂያ ሚኒስቴር አስታወቀ
(c) The Ethiopian News Agency