አዲስ አበባ, ሐምሌ 13 ቀን 2000 (አዲስ አበባ) - የግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ 116ኛ የልደት በዓል ዛሬ በልዩ ልዩ ዝግጀቶች ተከበረ፡፡በግርማዊነታቸው ስም የተሰየመው መታሰቢያ ድርጅት በትምህርታቸው ከፍተኛ ውጤት ላገኙና ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ገብቶ ለመማር የአቅም ማነስ ላለባቸው ለ150 ተማሪዎች የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን እስኪያገኙ ድረስ ስኮላርሽፕ መስጠቱን ገለፀ፡፡
የግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ መታሰቢያ ደርጅት ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ቀዳሚ ምክትል ሰብሳቢ ሊቀ ካህናት ዓባይነህ አበበ ዕለቱን በማስመልከት እንዳስታወቁት የበዓሉ መከበር ንጉሠ ነገሥቱ በህይወት ዘመናቸው የሠሯቸውን ሀገራዊና ዓለምአቀፋዊ ክንዋኔዎች የአሁኑ ትውልድ እንዲያውቅ ትልቅ ፋይዳ አለው፡፡
የንጉሠ ነገሥቱ የልደት ቀን የፊታችን ረቡዕ እንደነበር ያወሱት ምክትል ሰብሳቢው ሆኖም ዕለቱ የሥራ ቀን በመሆኑ የበዓሉ ታዳሚዎች በተረጋጋ መንፈስ እንዲያከብሩት ወደኋላ እንዲመጣ መደረጉን አመልክተዋል፡፡
በሐረር ኤጀርሳ ጎሮ ሐምሌ 16 ቀን 1884 ዓ.ም የተወለዱት ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ከአልጋ ወራሽነታቸው ጀምሮ ሥልጣን እስከለቀቁበት ድረስ ሀገራቸው በፖለቲካ፣ በምጣኔ ሀብትና በማህበራዊ ኑሮ መስክ የተሻለ ደረጃ ላይ እንድትደርስ የበኩላቸውን ጥረት ማድረጋቸውን ምክትል ሰበሳቢው ገልፀዋል፡፡
መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም በግፍ ከተገደሉ በኋላ አስከሬናቸው እንኳን በተዘጋጀለት ቦታ ሣያርፍ ሠዋራ ቦታ እንዲቆይ መደረጉን ያስታወሱት ሊቀ ካህናት ዓባይነህ በ1993 ዓ.ም በሕይወት ዘመናቸው ወዳሠሩት ቅድሥት ሥላሴ ካቴድራል እንዲያርፍ መደረጉን ጠቁመዋል፡፡
ሊቀ ካህናት ዓባይነህ እንዳሉት የግርማዊነታቸው መታሰቢያ ድርጀት ከ1995 ዓ.ም እስከ 1999 ዓ.ም ድረስ 150 ለሚሆኑ በትምህርታቸው ከፍተኛ ውጤት ላገኙና ረዳት ለሌላቸው ተማሪዎች ስኮላርሽፕ በመስጠት ራሳቸውንና ሀገራቸውን እንዲጠቅሙ አድርጓል፡፡
በአሁኑ ወቅት 50 ተማሪዎች ትምህርታቸውን እየተከታተሉ እንደሆነና ከነዚህ መካከል 26ቱ በዚህ ዓመት እንደሚመረቁም ጠቁመዋል፡፡
በአዲሱ በጀት ዓመት 120 ለሚሆኑ ተማሪዎች ዕድሉን ለመስጠት አስፈላጊው ዝግጅት መጠናቀቁን ምክትል ሰብሳቢው አስታውቀዋል፡፡
በበዓሉ ላይ ንጉሠ ነገሥቱ በህይወት ዘመናቸው ከሠሯቸው ዓበይት ክንዋኔዎች ጥቂቱ በፊልም ለታዳሚው ሕዝብ ለዕይታ ቀርቧል፡፡
በሥነ ሥርዓቱ ላይ ልዑላን ቤተሰቦች፣ የቀድሞ ከፍተኛ የጦር መኮንኖችና ሚኒስትሮች፣ ጥሪ የተደረገላቸው ዕንግዶችና የንጉሡ አፍቃሪዎች ተገኝተዋል፡፡
ስ 2፡30 መ 10፡00 ሪ 10፡10-11፡00 ኤ11፡37 የ11፡55 ድሰ9፡25 ጥ ከ
---END---