አዲስ አበባ, ነሐሴ 30 ቀን 1999 (አዲስ አበባ) - አዲሱን የኢትዮጵያ ሚሌኒየም በአል ለማክበር ከተለያዩ አለማት ከ500 በላይ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልድ ኢትዮጵያውያንና የውጭ አገራት ዜጎች ትናንት ማምሻውን አዲስ አበባ ገብተዋል፡፡ለእንግዶቹ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የፈረሙበት የእንኳን ደህና መጣችሁ የመልካም ምኞች መግለጫ ካርድና አበባ ተበርክቶላቸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በመልካም ምኞት መግለጫቸው ላይ እንዳሰፈሩት ኢትዮጵያ ተስፋ ሰጪ በሆነ የልማት ጎዳና ላይ ትገኛለች፡፡
በአሉን ለማክበር የምትመጡ ኢትዮጵያውያን ሙያዊና ቁሳዊ እገዛ ከታከለበት ደግሞ ኢትዮጵያ ይበልጥ ትበለጽጋለች ብለዋል፡፡ ለኢትዮጵያ እድገትም የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ለእንግዶቹ ግብዣ አቅርበዋል፡፡
ትናንት ማምሻውን አዲስ አበባ ከገቡት እንግዶች መካከል የአሜሪካ ሚኖሶታ ነዋሪ የሆነው ዳኛቸው ጉደታ እንደገለጸው በአሉን ለማክበር ወደ አገሩ በመምጣቱ ተደስቷል፡፡ ለብሄራዊ ሚሌኒየም ጽህፈት ቤት 30 የሚጠጉ መጽሃፍትን በስጦታ ለማበርከት መዘጋጀቱንም አመልክቷል፡፡
ሁሉም ያለፈውን ጊዜ በመርሳት አዲሱን ሚሌኒየም በመቻቻልና በመደጋገፍ ሊያከበረው እንደሚገባ አሳስቧል፡፡
ሌላው የአሜሪካ የሜይን ፖርትላንድ ነዋሪ የሆኑት አቶ አረፍአይኔ የኔነህ በበኩላቸው ወደ ኢትዮጵያ የመጡት የሚሌኒየም በአሉን ለማክበር ነው፡፡ በኢትዮጵያ ቆይታቸውም የተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮችን እንደሚያጠኑ ገልጸዋል፡፡
ላለፉት 12 አመታት በቦስተን ነዋሪ የሆነችው ሙሉ ጥላሁን ለበአሉ ወደ አገሯ በመመለሷ መደሰቷን ገልጻ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚሌኒየሙን አጋጣሚ በመጠቀም ለለውጥ እንዲነሳ ጥሪ አቅርባለች፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ለሚሌኒየሙና ከውጭ ለሚመጡ እንግዶች ልዩ ትኩረት በመስጠት በፊርማቸው ያበረከቱት የመልካም ምኞት መግለጫ ካርድ ልዩ ስሜት እንዳሳደረባት ገልጻለች፡፡ ይህም በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያው መሆኑን ጠቁማለች፡፡
ለእንግዶቹ በቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ በመገኘት ደማቅ አቀባበል ያደረጉላቸው የአዲስ አበባ ሚሌኒየም ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ኪሮስ ሃይለ ስላሴ እንደገለጹት ጽህፈት ቤቱ ለእንግዶቹ የሚያደረገው አቀባበል እስከ መጪው ሰኔ ወር 2000 ዓም ድረስ ይቀጥላል፡፡
---END---