አዲስ አበባ, ጥቅምት 15 ቀን 2000 (አዲስ አበባ) - የኢትዮጵያ መድሀኒት አስተዳዳርና ቁጥጥር ባለስልጣን ማኔጅመንት ሳይንስ ፎር ሄልዝ አር .ፒ.ኤም ፕላስ ከተባለ የአሜሪካ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ጋር በጋራ ለመስራት የሚያስችል የአምስት ዓመት የውል ስምምነት ተፈራረመ፡፡በቅርቡ አዲስ አበባ ውስጥ የተካሄደውን ይህንኑ ስምምነት የፈረሙት የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀይለስላሴ ቢሆንና የማኔጅመንት ሳይንስ ፎር ሄልዝ አር.ፒ.ኤም ፕላስ ቺፍ ኢን ፓርቲ ዶክተር ንጉሱ መኮንን ናቸው፡፡
የባለስልጣኑ መስሪያ ቤት ዛሬ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጸው ስምምነቱ በመድሀኒት ዘርፍ መልካም አስተዳዳርን ለማስፈን፣ በአገሪቱ ጤና አገልግሎት ጥቅም ላይ የሚውሉ መድሀኒቶች ደህንነታቸው፣ ፈዋሽነታቸውንና ጥራታቸውን የማረጋጋጥ አቅም ለመገንባት ያስችላል፡፡
በተጨማሪም ስምምነቱ መድሀኒቶቹ በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ለማድረግና የመድሀኒት አቅርቦት ማኔጅመንት ስርዓት ለማጠናከር እንዲሁም ጸረ ተህዋስያን መድሀኒቶች በተለያዩ ተህዋስያን በመለማማድ የፈዋሽነታቸውን አቅም እንዳያጡ ለመከላከልና ለመግታት የሚያስችሉ ስትራቴጂዎችን በመቅረጽ ስራ ላይ ለማዋል የሚረዳ ነው፡፡
ስምምነቱ መስሪያ ቤቱ በየዓመቱ የሚያቀርበውን እቅድ ተግባራዊ ለማድረግ በገንዘብ፣ በማቴሪያልና በቴክኒክ ረገድ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማግኘት ያስችለዋል፡፡
ሁለቱ መስሪያ ቤቶች በኢትዮጵያ የመድሀኒት አሰተዳደር ዘርፉን ለማጠናከር በቅንጅት ለመንቀሳቀስ የጋራ ሀላፊነት እንዳለባቸውም በውል ስምምነቱ ላይ ተቀምጧል፡፡
በተጨማሪም አካላቱ በተስማሙባቸው በስትራቴጂክ እቅድ የተቀመጡ ቁልፍ እቅዶችን ለማስፈጸምና ከተያዘው ከሚሌኒየሙ ጀምሮ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል ከ17 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት መያዙን ባለስልጣኑ ገልጿል፡፡
የአምስት ዓመቱ እቅድ ከ2000 እስከ 2004 የሚከናወን ሲሆን በቀጣይነትም መስሪያ ቤቱ ዘርፉን ለማጠናከር ሌሎች በርካታ ፕሮጀክቶችን ነድፎ ከሌሎች መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጋር በጋራ አጠናክሮ እንደሚሰራ አስታውቋል፡፡
---END---