አዲስ አበባ, ጥቅምት 15 ቀን 2000 (አዲስ አበባ) - በኢትዮጵያ በቤተሰብ ደረጃ የውሃ አስተዳደርን በማጠናከር የውሃ ወለድ በሽታዎችን መቀነስ በሚቻልበት መንገድ ዙሪያ የሚነጋገር ዓለም አቀፍ ጉባኤ በመጪው ሳምንት አዲስ አበባ ውስጥ አንደሚካሄድ የዓለም ጤና ድርጅት አስታወቀ፡፡የዓለም ጤና ድርጅት ዛሬ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላከው መግለጫ እንዳመለከተው በመጪው ሰኞ የሚጀምረው የሁለት ቀናት ጉባኤ የሚካሄደው በአዲስ አበባ ሂልተን ሆቴል ሲሆን የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ይሳተፋሉ፡፡ ጉባኤው የተዘጋጀው በዓለመ ጤና ደርጅት አማካኝነት መሆኑንም አመልክቷል፡፡
የጉባኤው ተሳታፊዎች በቤተሰብ ደረጃ የውሃ ንፅህናን ለማስጠበቅና ደህንነቱ የተጠበቀ አያያዝን ለማጠናከር በሚቻልበት ስልት እንደሚነጋገሩ ድርጅቱ ገልጿል፡፡
በዚህም በአሁኑ ወቅት ያለውን የውሃ አያያዝ ስርዓት በተሻለ ደረጃ በመገንባት ከአገራዊው የውሃ፣ የግልና የአካባቢ ንፅህና አጠባበቅ ስትራቴጂ ጋር የተጣጣመ እንዲሆን ማድረግ የሚያስችል ሁኔታ እንደሚፈጠር አስረድቷል፡፡
የቤተሰብ ደረጃ የውሃ ንፅህና አጠባበቅና አያያዝ ስርዓት የመጠጥ ውሃ ጥራትን በከፍተኛ ደረጃ የሚያሻሽለው ከመሆኑም በላይ ተቅማጥን የመሰሉ የውሃ ወለድ በሽታዎች መጠንን ይቀንሳል ሲል የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል፡፡
በተለይ ይህ ስርዓት የውሃ አቅርቦታቸው በተበከሉ ወንዞች፣ ሃይቆችና በአንዳንድ ሰፍራዎችም ደህንነታቸው ያልተጠበቀ ጉድጓዶች የሆኑትን የህብረተሰብ ክፍሎች ህይወትን በከፍተኛ መጠን ያሻሽለዋል ሲል አመልክቷል፡፡
በአገር ደረጃ ሲካሄድ በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነው ይህ ጉባኤ በኢትዮጵያ መዘጋጀቱ የቤተሰብ የውሃ ንፅህና አጠባበቅና አያያዝ ስርዓት ጉዳይ ትኩረት እንዲሰጠው ለማድረግና ደህንነቱ የተጠበቀ የመጠጥ ውሃን ለማስፋፋት የሚደረገውን ጥረት የበለጠ ለማጠናከር የሚያስችል አጋጣሚን እንደሚፈጥር ድርጅቱ ገልጿል፡፡
ከዞህም ሌላ ጉባኤው የኢትዮጵያ መንግስት ውሃን ለሁሉም ለማዳረስ የተያዘውን ዩኒቨርሳል አክሰስ እቅድን አውን ለማድረግ ለጀመረው ጥረትም አጋዥ እንደሚሆን ጠቁሟል፡፡
---END---