መድሃኒት አስተዳደር, ጥቅምት 15 ቀን 2000 (አዲስ አበባ) - የኢትዮጵያ መድሀኒት አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን የአደገኛ መድሀኒቶችና እጾች ህገወጥ ዝውውርና አጠቃቀምን ለመከላከልና ለመቆጣጣር የሚያስችል የአምስት ዓመት መሪ እቅድ ማዘጋጀቱን አስታወቀ፡፡በኢትዩጵያ በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነ ብሄራዊ የመድሀኒት ፎርሙላሪ ማዘጋጀቱንም ገልጿል፡፡
በባለስልጣኑ የሲቪል ሰርቪስ ማሻሻያና የህዝብ ግንኙነት አገልግሎት ኋላፊ አቶ አማረ አሰፋ ዛሬ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት
ይኽው የአምስት አመት መሪ እቅድ በተያዘው ሚሌኒየም በተግባር ላይ ይውላል፡፡
መሪ እቅዱ የአደገኛ መድሀኒቶችና እጾች ህገወጥ ዝውውርና አጠቃቀም የሚገኝበትን ሁኔታ በጥልቀት በመገምገም ጠንካራና ደካማ ጎኖችን እንዲሁም ቁልፍ የሆኑ ችግሮችን በመለየት ራእይና ተልእኮ ያስቀመጠ ነው፡፡ በተጨማሪም ራእይና ተእልኮውን ዳር ለማድረስ የሚያስችሉ ቁልፍ ስትራቴጂዎችንም በዝርዝር ይዟል፡፡
ይህም እየተካሄደ ያለውን የአደገኛ መድሀኒቶች ህገወጥ ዝውውር የመከላከልና የመቆጣጣር ስራን ውጤታማ እንደሚያደርገው የህዝብ ግንኙነት አገልግሎት ኋላፊው ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ ይህን ዓለም ዓቀፍና አገር አቀፍ ችግር ለመከላከልና ለመቆጣጣር አለም አቀፍ የሆኑ ሶስት ስምምነቶችን ተቀብላላች፡፡
በዚህም ረገድ ፖሊሲዎችን በመቅረጽና ነባር ህጎችን በማሻሻል አስፈጻሚ አካላትን በየደረጃው በማደራጀት የህብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ እየተደረገ ያለው ጥረት አሁንም ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል፡፡
ከዚሁ በተጨማሪ ባለስልጣኑ ያዘጋጀው ብሄራዊ የመድሀኒት ፎርሙላሪ በሁሉም ደረጃ ላሉ የጤና ድርጅቶችና የጤና ባለሙያዎች አገልግሎት ሊሰጥ የሚችል ነው፡፡
ቀደም ሲል ከወረዳ በላይ ላሉ የጤና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ፎርሙላሪ ያልነበራቸው መሆኑን ገልጸው አሁን የተዘጋጀው ብሄራዊ ፎርሙላሪ በአገሪቱ ላሉ የጤና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ባሉበት ደረጃ በፍጥነት መረጃ ለማግኘት የሚያስችላቸው እንደሆነም አቶ አማረ አመልክተዋል፡፡
ፎርሙላሪው ለማንኛውም ባለሙያ አጠቃላይ የመረጃ ምንጭ ሆኖ ከማገልገል በተጨማሪ ባለሙያው ስለማንኛውም መድሀኒት መረጃ ሲፈልግ የመድሀኒት ፎርሙላሪውን በማጣቀሻነት ሊጠቀም እንደሚችል ገልጸዋል፡፡
---END---