አዲስ አበባ, ጥቅምት 13 ቀን 2000 (አዲስ አበባ) - የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ድርጅት ኢጋድ ከመጪው ሰኞ ጀምሮ ለሦስት ቀናት የሚቆይ በቅድመ ግጭት ማስጠንቀቂያና ምላሽ ላይ ያተኮረ ስብሰባ በሱዳን ካርቱም ውስጥ እንደሚያካሂድ አስታወቀ፡፡አምስተኛው የኢጋድ የቅድመ ማስጠንቀቂያ የቴክኒክና ሰባተኛው የቋሚ ፀሐፊዎች ኮሚቴ ስብሰባ የሚካሄደው በቅድመ ግጭት ማስጠንቀቂያ ተግባራት ላይ የተካሄዱትን ዕንቅስቃሴዎች ገለጻ ለማድመጥና ከ2007 እስከ 2011 ድረስ ሊተገበር ለታቀደው የቅድመ ግጭት ማስጠንቀቂያ ስትራተጂ አፈጻጸም ላይ ለመወያየት ነው፡፡
ድርጅቱ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዛሬ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው በስብሰባው ላይ የቅድመግጭት ማስጠንቀቂያ ቴክኒክ ኮሚቴ አባላትና የኢጋድ አባል ሃገራት የሆኑት የኢትዮጵያ፣የጅቡቲ፣የኬንያ፣የሱዳን፣የሶማሊያና የኡጋንዳ ቋሚ ፀሐፊዎች ተካፋይ ይሆናሉ፡፡
የኢጋድ የቅድመማስጠንቀቂያና አፋጣኝ ምላሽ መስጫ /ሲዋርን/ በፈረንጆቹ 2000 ላይ በአባል ሃገራቱ የተመሠረተ ሲሆን ዓላማውም የግጭት መንስዔዎችን አስቀድሞ መረጃ በመስጠት በአህጉሪቱ ለሚከሰቱ ግጭቶች አፋጣኝ ምላሽ መስጠት ማስቻል ነው፡፡
ሲዋርን ሥራ የጀመረው እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ2003 እንደሆነም መግለጫው አመልክቷል፡፡
ኢጋድ የመረጃ ምንጮቹን በማስፋት፣ የምላሽ አሰጣጥ ፍጥነቱን በማሻሻልና የግንኙነት መረቡን በማስፋት ቀጣይነት ያለው ጥናት እንዲሁም የስልጠናና የአስተዳደር ሥራዎችን በመሥራት ላይ እንደሚገኝም መግለጫው ጠቁሟል፡፡
ሪ11፡45 የ 1፡02 ጥ ከ
---END---