አዲስ አበባ, ጥቅምት 13 ቀን 2000 (አዲስ አበባ) - የጥራት ደረጃውን ሳያሟላ የሚመረት ብሎኬት በግንባታ ላይ አደጋ ስለሚያስከትል በግብይት ወቅት ገዢዎች አምራች ድርጅቱ ወቅታዊ የጥራት ማህተም ፈቃድ ተጠቃሚ መሆኑን ሊያረጋግጡ እንደሚገባ የጥራትና የደረጃዎች ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በስፋት በመካሄድ ላይ ያለው የቤቶች ግንባታ ሥራ ውጤታማነቱ እንዲጠናከር ለግንባታ ግብዓትነት የሚቀርበው ብሎኬት ጥራቱ የተጠበቀ መሆን እንዳለበትም አመልክቷል፡፡
በባለሥልጣኑ የሕዝብ ግንኙነትና ትምህርት አገልግሎት ኃላፊ አቶ ሢሳይ አሰፌ ዛሬ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት አንዳንድ የብሎኬት አምራች ድርጅቶች የኅብረተሰቡን የመግዛት አቅም በማየት ብቻ ደረጃውን ያልጠበቀ ምርት በማምረት በአነስተኛ ዋጋ እንደሚሸጡ ጠቁመዋል፡፡ይህ ጉዳይ በዜጐች ደህንነትና በአገር ኢኮኖሚ ላይ አደጋ የሚያስከትል መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ከ1999 ዓ.ም በፊት በብሎኬት አምራችነት የተሰማሩና የጥራት ማህተም ፊቃድ ተጠቃሚ የሆኑ ድርጅቶች ከ10 እንደማይበልጡ የጠቆሙት ኃላፊው በአሁኑ ወቅት በአጠቃላይ 408 የብሎኬት አምራች ድርጅቶች የጥራት ማህተም ፈቃድ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ከነዚህ መካከልም 209 በአዲስ አበባ፣ ቀሪዎቹ በኦሮሚያ፣ በትግራይ፣ በአማራና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልሎች እንደሚገኙ አመልክተዋል፡፡
በአሁኑ ጊዜ ብዙዎቹ ድርጅቶች የምርቶቻቸውን ጥራት ለማረጋገጥ ከድርጅቱ የጥራት ማህተም ፈቃድ እንዲሰጣቸው በመጠየቅ ላይ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡
ኃላፊው እንዳሉት ተጠቃሚዎች አምራች ድርጅቱ ወቅታዊ የጥራት ማህተም ፈቃድ ያለው መሆኑን ማረጋገጣቸው ለግንባታ ሥራቸው የተሻለ ዋስትና ያስገኝላቸዋል፡፡
ግንባታ እያካሄዱ ያሉ ግለሰቦች በብሎኬት ግብይት ወቅት ጥራት ላለው ምርት ልዩ ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው ያሳሰቡት አቶ ሲሳይ በዚህ ሳቢያ የሚደርሰውን ጉዳት ለመከላከል በግብይት ወቅት የዋጋ ቅናሽን ብቻ ከማየት ይልቅ ለምርት ጥራት ቅድሚያ ትኩረት በመስጠት በአገርና በሕብረተሰቡ ላይ የሚደርሰውን ኪሣራ መከላከል ይገባል ብለዋል፡፡
ሪ8፡30፣ያ፡8፡55 ኤ1 11፡30 የ12፡25
---END---