አዲስአበባ, ጥቅምት 13 ቀን 2000 (አዲስ አበባ) - በዳርፉር የአፍሪካ ሕብረተና የተባበሩት መንግስታት የተቀናጀ የሰላም አስከባሪ ተልዕኮ በቅርቡ መሉ ለሙሉ እንደሚሰማራና በአሁኑ ወቅትም ሁኔታዎች መመቻቸታቸውን የአፍሪካ ሕብረት የሰላምና ጸጥታው ምክርቤት አስታወቀ፡፡የሰላምና ጸጥታ ምክርቤቱ በዳርፉር ጉዳይ ላይ ትናንት አዲስ አበባ ወስጥ ከተሰበሰበ በኋላ የጋራ መግለጫ አውጥቷል፡፡
የምክር ቤቱ የወቅቱ ሊቀመንበር የአንጎላ አምባሳደር አማኑኤል አውጉስቶ ስብሰባው ሲያበቃ እንደገለጹት በዳርፉር የሰላም አስከባሪ ኃይል ለማሰማራት የተለያዩ ቅድመ ስራዎች በመገባደድና በመልካም ሁኔታ ላይ ይገኛሉ፡፡ በዳርፉር ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ አስመልከቶ የቀረበለትን ሪፖርት ምክርቤቱ መመርመሩን ጠቁመዋል፡፡
በሥፍራው የተባበሩት መንግስታትና የአፍሪካ ሕብረት የተቀናጀ የሰላም አስከባሪ ተልዕኮ በሚሰማራበት ሁኔታና በቅርቡም በትሪፖሊ ስለሚደረገው የፖለቲካ ውይይት የቀረበው ማብራሪያንም እንደተቀበለው ተናግረዋል፡፡
ምክርቤቱ በዳርፉር የአፍሪካ ሰላም አስከባሪ ሰራዊት ላይ በቅርቡ የደረሰው አሰቃቂ ጥቃት ምክርቤቱ እንዳሳዘነው ገልፀው ለማቾቹ ቤተሰቦችና አገራት መጽናናትን ተመኝተዋል፡፡
በዳርፉር ጠንካራ የሰላም አስከባሪ ኃይል ለማሰማራትና ተልዕኮውንም ለማሳካት የተባበሩት መንግስታት የመሪነቱ ሚና በመወጣት አስፈላጊውን ሃብት ማሰባሰብ አለበት ብለዋል፡፡
የመንግሰታቱ ድርጅት ዓለምአቀፍ ሰላምና ጸጥታ እንዲሰፍን የቅድሚያ ኃላፊነቱ መሆኑን አምባሳደሩ ጠቁመው በዳርፉር የተባበሩት መንግሰታትና የአፍሪካ ሕብረት ተልዕኮ ''ዩኤን አሚድ'' አቅም ለማጎልበት የመንግስታቱ ድርጅት ድጋፍ መጨመር እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በዳርፉር የተሰማራው የአፍሪካ ሕብረት የሰላም አስከባሪ ኃይል /ኤሚስ/ ከአፍሪካ ውጭ ካሉአገሮች የሚውጣጣ የፖሊስ ኃይል፣ ወታደራዊ ሰራዊትእና ሌሎች አካላት ጋር ተቀናጅቶ እንደሚሰራም ገልጸዋል፡፡
የዩኤን አሚድ ሰራዊት አዛዥ ጋናዊው ጄነራል ሄኒሪ አንዪዶ እንደገለጸት በስፍራው ከሚሰማራው የሰላም አስከባሪ ተልእኮ 90 በመቶው ለማማላት ቃል ተግብቷል፡፡
በአብዛኛው ከ23 አገራት የሚውጣጣ አፍሪካዊ ሰላም አስከባሪ ሰራዊትና ድጋፍ ሰጪ አካላት በስፍራው እንደሚሰማሩ ምክርቤቱ ጠቁሞ ቀሪዎቹ ወደስፍራው የሚላኩት ደግሞ ከ19 አፍሪካዊ ካልሆኑ አገራት የተውጣጡ መሆናቸውን አመልከቷል፡፡
---END---