አዲስ አበባ, ነሐሴ 18 ቀን 1999 (አዲስ አበባ) - መንግሥት የውኃውን ክፍለ ኢኮኖሚ ለማሳደግ የሚያደርገው ጥረት በባለድርሻዎች ከተደገፈ ጥረቱ ዘላቂና ውጤታማ እንደሚሆን የውኃ ሀብት ሚኒስቴር ዴኤታ አሰታወቁ፡፡የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ለአንድ ቀን ያዘጋጀውን ሀገር አቀፍ የውኃ ክፍለ ኢኮኖሚ ጥናት የባለሙያዎች ምክክር አውደ ጥናት ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ ሲጀመር ሚኒስትር ዴኤታው አቶ አዱኛ ጀቤሳ እንዳስታወቁት የሀገሪቱን የውኃ ሀብት በአግባቡ ከጥቅም ላይ ለመዋል የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ያዘጋጀው በምርምር ላይ የተደገፈ የምክክር ውይይት መንግስት በዘረፉ የጀመረውን ጥረት ያጠናክራል፡፡
ሚኒስትር ዴኤታው እንዳሉት የምክክር አውደ ጥናቱ በሀገር አቀፍና በክልሎች እየተተገበረ ላለው ሥልት መረጃ ከመስጠቱም በላይ የሀገሪቱን የውኃ ሀብት ልማት ለማሳደግ የባለድረሻዎች አስተዋጸኦ የላቀ ነው፡፡
ዩኒቨርሲቲው በውኃው ከፍለ ኢኮኖሚ ላይ ተመርኩዞ ያቀረበው የምክክር ጥናት በውኃው ከፍለ ኢኮኖሚ ልማት ላይ ያለውን እንቅፋት መለየት፣ ለውኃው ከፍለ ኢከኖሚ ልማት የሚያስፈጉትን ሥልጠናዎች፣ ምርምርና ትምህርት ቅድሚያ ሰጥቶ መለየትና ፈጻሚ አካላት የውኅውን ክፍለ ኢኮኖሚ ልማት በተሻሻለና ዘላቂ በሆነ መንገድ የሚተገበሩበት ሁኔታ እንደሚያመቻች ሚኒስትር ዴኤታው አመልክተዋል፡፡
በውሃው ክፍለ ኢኮኖሚ ልማት በኩል አቅምን ለመገንባትና ዘላቂነትን ለማምጣት ውይይቱ ጠቃሚ መሆኑን ያመለከቱት ሚኒስትር ዴኤታው ከውይይቱ ማጠቃላይ ጠንካራ የሆነ አስተሳሰብ ሊፈልቅ እንደሚችል ገልጸዋል፡፡
የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክና ምርምር ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ቦጋለ ገብረማርያም በበኩላቸው አውደ ጥናቱ የኢትዮጵያውያንን የኑሮ ሁኔታ የተሻለ ለማድረግ የተጀመረውን ጥረት ወደፊት ለማራመድ ወሳኝነት አለው፡፡
ምክትል ፕሬዚዳንቱ እንዳሉት የአርባ ምንጭ ዩኒቨረስቲ ፍላጎት በውኃው ክፍለ ኢኮኖሚ በምሥራቅ አፍሪካ ብቃት ያለው ማእከል ሆኖ መገኘት ነው፡፡
በአውደ ጥናቱ ላይ በውኃው ዘርፍ ብቃትና ቁርጠኝነት ያላቸው ባለሙያዎችና ባለድርሻዎች የተሳፉ ሲሆን ውይይቱ ባለሙያዎቹ ልምዳቸውን የሚለዋወጡበት እደሚሆንም ዶክተር ቦጋለ አስታውቀዋል፡፡
በአውደ ጥናቱ ላይ ከፌዴራል ውኃ ሀብት ሚኒስቴርና ከሁሉም ክልሎች የውኃ ቢሮ የተውጣጡ ከ50 በላይ ባለሙያዎች ተካፍለዋል፡፡
---END---