የኢትዮጵያ ሚሌኒዬም በአል የአገሪቱን ብቻ ሳይሆን መላው አፍሪካን እስመልክቶ በአለም ሀዘብ ዘንድ ያለውን የተሳሳተ ግምት የሚያስቀይር ነው - ኒው አፍሪካ
አዲስ አበባ, ነሐሴ 18 ቀን 1999 (አዲስ አበባ)

በመከበር ላይ ያለው የኢትዮጵያ ሚሌኒዬም በአል የአገሪቱን ብቻ ሳይሆን መላው አፍሪካን በሚመለከት በአለም ህዝብ ዘንድ ያለውን የተሳሳተ ግንዛቤ ለማስቀየር የሚያስችል ነው ሲል ኒው አፍሪካ መፅሄት ዘገበ ፡፡

ኒው አፍሪካ መፅሄት " በኢትዮጵያ የሶስተኛው ሚሌኒዬም በአል አከባበር " በሚል ርእስ ትናንት ባወጣው ዘገባ ላይ እንዳመለከተው የኢትዮጵያ ሚሌኒዬም የአፍሪካን እምቅ ባህል ገፅታ ለአለም ህብረተሰብ የሚስተዋውቅ ኢትዮጵያ ጠብቃ ያቆየችው ልዩ በአል ነው ፡፡

ኢትዮጵያ የሚሊነዬም በአሏን እያከበረች ባለችበት በአሁኑ ወቅት እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ1868 የእንግሊዝ ጦር የመቅደላ ከተማን በርካታ ታሪካዊና ባህላዊ ቅርሶች ዘርፎ በወሰደበት ወቅት ወደ እንግሊዝ የተወሰደውንና ህይወቱ እዚያው ያለፈውን የአፄ ቴዎድሮስ ልጅ የልኡል አለማየሁ አፅም እንዲመለስላትም አጥብቃ እየጠየቀች ነው ሲል መፅሄቱ ዘግቧል፡፡

ነዋሪነታቸው በእንግሊዝ አገር ከሆኑ ኢትዮጵያውያን የተወለደውና በአሁኑ ወቅት የዘጠኝ አመት ታዳጊ ወጣት የሆነው ተማሪ ገብርኤል ካሳዬ በቅርቡ ስልጣናቸውን ለተተኪያቸው ላስተላለፉት ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ብሌይር " እኛ ኢትዮጵያውያን አዲሱን የአገራችንን ሚሌኒዬም በአል በማክበር ላይ በምንገኝበት በአሁኑ ወቅት በእንግሊዝ አገር የሚገኙ የኢትዮጵያን ታሪካዊ ቅርሶች አገርዎ እንድትመልስ የሚያስችል ወሳኝ እርምጃ እንዲወስዱ እንጠይቃለን " በማለት የፃፈውን ደብዳቤ በአብነት አስፍሯል፡፡

ታዳጊ ወጣቱ በደብዳቤው አያይዞም "በእንግሊዝ አገር የምንገኝ እኛ የኢትዮጵያውያን ልጆችና የኢትዮጵያውያን ወዳጆች የእንግሊዝ መንግስት የኢትዮጵያን ቅርሶች በመመለስ የመሪነቱን ስፍራ እንዲይዝ እንመኛለን" ማለቱን ይገልፃል፡፡

ይህን ታዳጊ ወጣት ጨምሮ በአለም ዙሪያ ያሉ ኢትዮጵያውያንና ደጋፊዎቻቸው የአፍሪካ ህብረት "የአፍሪካውያን ሚሊኒዬም " በሚል ያፀደቀውን የሚሌኒዬም በአላቸውን በማክበር ላይ ይገኛሉ ሲል ዘገባው አመልክቷል፡፡

በጁሊያን የዘመን አቆጣጠር በምትመራው ኢትዮጵያ አንድ አመት 13 ወራት አሉት ያለው ዘገባው የአገሪቱ ዘመን አቆጣጠርም ከምእራባውያን በእጅጉ የተለዬ ነው ብሏል፡፡

የተማሪ ገብርኤል ደብዳቤ " በዩናይትድ ኪንግደም ከ140 አመት በፊት በአፄ ቴዎድሮስ ዘመን የእንግሊዝ ጦር አገሪቱን በወረረበት ወቅት የዘረፋቸው ጥንታዊ ፅሁፎች፣ የነገስታት ዘውድ ፣የቤተክርስቲያናት ቅርሶችና መስቀሎች እንደሚገኝ ጠቅሶ ከአለም አገራትም የኢትዮጵያ በርካታ ታሪካዊ ቅርሶችን በማከማቸት ዩናይትድ ኪንግደም ተጠቃሽ መሆኗን ያመለክታል፡፡

ለገብርኤልና በአለም ዙሪያ ላሉ ሌሎች የኢትዮጵያ ታዳጊ ወጣቶች የኢትዮጵያ ሚሌኒዬም አገሪቱን በአለም ህዝብ ፊት እንደገና በበጎ ገፅታዋና በታሪካዊ ቅርሶቿ እንድትታወቅ የሚያደርጋት የተሃድሶ ዘመንዋ ነው ያለው ዘጋቢው ታዳጊ ወጣት ገብርኤል የአገሪቱን ታሪካዊ ቅርሶች መመለስን አስመልክቶ ለጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ብሌይር ደብዳቤ የፃፈበትም ምክንያት ይኸው እንደነበር አመልክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ታሪካዊ ቅርሶች በእንግሊዝ አገር መቀመጥ ለእንግሊዛውያን ታሪካዊም ሆነ ባህላዊ ጠቀሜታ የለውም ያለው ይኸው ታዳጊ ወጣት እነዚህ ቅርሶች ለኢትዮጵያውያን ቢመለሱ ግን የበለፀገ ታሪካቸውና ባህላዊ እሴታቸው አካል የሆኑ በዋጋ የማይተመኑ መለያዎቻቸው ናቸው ብሏል፡፡

የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ ኢትዮጵያ በማክበር ላይ ባለችው የሚሊኒዬም በአል የልዑል አለማየሁ ቴዎድሮስ አፅም ወደ አገሩ ተመልሶ በክብር አንዲያርፍ ለእንግሊዟ ንግስት ኤልሳቤጥ ሁለተኛ በፃፉት ዳብዳቤ ላይ ይፋ ጥያቄ ማቅረባቸውንም አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ሚሊኒዬም በአል አከባበር ምክርቤት ፅህፈት ቤት ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የህዝብ ግኑኝነት ወይዘሮ ነፃነት አስፋው " የልኡል አለማየሁ አስከሬን በትከክለኛው ቦታ ማለትም ወደ አገሩ መጥቶ በክብር ማረፍ ይኖርበታል ማለታቸውን ኒው አፍሪካ ዘግቧል፡፡

የኢትዮጵያ ሚሊኒዬም በአል አከባበር "በሁሉም ዜጋ መካከል ብሔራዊ መግባባትን በመፍጠር ፖለቲካዊ ጥንካሬ ያላት በኢኮኖሚ የበለፀገች ኢትዮጵያን እውን ማድረግ "የሚል መርህ እንዳለው ያመለከተው ዘገባው በአሁኑ ወቅት የበአሉ አከባበር የአገሪቱ ሙዚቀኞች፣ የስነጥበብ ሰዎችና ደራሲዎችን ጨምሮ ሁሉም ዜጋ በአንድ መንፈስ እንዲንቀሳቀሱ እያደረገ ነው ብሏል፡፡

ከአሜሪካ በሚሊኒየሙ በአል አከባበር ላይ ለመገኘትና የዘፈን ዝግጅቱን በነፃ ለማቅረብ ወደ ኢትዮጵያ የመጣው አርቲስት አያሌው መስፍን " የሚሌኒየሙ በአል ሰላምን በማስፈንና ብሔራዊ መግባባትን በመፍጠር በአገሪቱ የሚካሄደውን ልማት ለማስቀጠል ወሳኝ አጋጣሚን የፈጠረ ነው" ሲል እንደገለፀለት የመፅሄቱ ዘጋቢ አመልክቷል፡፡

የሚሌኒየሙ በአል ታዳጊ ወጣት ገብርኤል ካሳዬን ጨምሮ ከኢትዮጵያ ውጭ የሚኖሩ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን በአገራቸውና ቱሪስቶችንም ከመላው አለም ያሰባስባል ተብሎ እንደሚጠበቅም መፅሄቱ ገልጿል፡፡

የበአሉ አዘጋጆች የሚሌኒዬም በአሉ ለአፍሪካውያን የተስፋ፣ የቁርጠኝነት የእድገትና የብልፅግና ይሆናል የሚል እምነት እንዳላቸውም ዘገባው ጠቁሟል፡፡

በመላው አለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በአሁኑ ወቅት የሚሌኒየም በአሉን ምክንያት በማድረግ በአገሪቱ ክሊኒኮችንና ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት የሚያስችል ገቢ እያሰባሰቡ መሆኑንም ገልጿል፡፡

---END---

Headlines
የሚሌኒየሙ በዓል አፍሪካውያን ካለፈው ዘመን የተሻለ ሰላም፣ ነፃነትና ተባብረው በመስራት ከፍተኛ ውጤት ለማምጣት ጉልህ አስተዋጽኦ
የኢትዮጵያ ሚሌኒዬም በአል የአገሪቱን ብቻ ሳይሆን መላው አፍሪካን እስመልክቶ በአለም ሀዘብ ዘንድ ያለውን የተሳሳተ ግምት የሚያስቀይር ነው - ኒው አፍሪካ
የሐረሪ ክልል አንደኛ መደበኛ ጉባኤ ከ172 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት አጸደቀ
መንግሥት የውኃውን ክፍለ ኢኮኖሚ ለማሳደግ የሚያደርገው ጥረት በባለድርሻዎች መተደገፈ አለበት
(c) The Ethiopian News Agency